አማርኛ

ሕሊናን መመርመር፦ አሥርቱ ትእዛዛት

አንደኛው ትእዛዝ፦ “እኔ ጌታ አምላክህ ነኝ፤ ከእኔ በፊት ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።” 

እግዚአብሔርን ክጄአለሁ? በሌሎች ፊት በእምነቴ አፍሬአለሁ ወይም እምነቴን ክጄአለሁ? በቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ወይም ልማዶች ላይ ተሳልቄአለሁ? ጸሎቴን ቸል ብያለሁ? ጥንቆላ፣ ዊካ ወይም ሌሎች ድብቅ መንፈሳዊ ኃይሎችን ለመጠቀም የሚደረጉ ሥራዎችን ተጠቅሜአለሁ? እንደ ዕድል ገላጮች፣ ከሙታን መናፍስት ጋር የሚያገናኙ ሰዎች፣ መናፍስትን ለማነጋገር የሚያገለግሉ የዊጃ ሰሌዳዎችና የታሮት ካርዶች ያሉ የተለያዩ አጉል እምነቶችን ተከትያለሁ?

ሁለተኛው ትእዛዝ፦ “የጌታን ስም በከንቱ አትጥራ።” 

የእግዚአብሔርን ስም በቸልታ፣ በቁጣ ወይም በመደነቅ እጠራለሁ? በማንኛውም ሰው ወይም ነገር ላይ ክፉ እንዲወርድ ረግሜአለሁ?

ሦስተኛው ትእዛዝ፦ “የሰንበትን ቀን ቀድስ።”

በራሴ ጥፋት በየእሑዱና ቅዳሴ መሳተፍ ግዴታ በሆነባቸው በሁሉም ቅዱሳን በዓላት በቅዳሴ ከመሳተፍ ቀርቻለሁ? ያለ በቂ ምክንያት ወደ ቅዳሴ አርፍጄ እደርሳለሁ ወይም ቀድሜ እወጣለሁ? በቅዳሴ ጊዜ ሐሳቤ እንዲበታተን እፈቅዳለሁ?

አራተኛው ትእዛዝ፦ “አባትህንና እናትህን አክብር።” 

ወላጆቼን አልታዘዝ ብያለሁ ወይም ንቄአቸዋለሁ? ያረጁ ወላጆቼን ቸል ብያለሁ? ለቤተሰቤ አክብሮት፣ ጨዋነት ወይም ትሕትና ይጎድለኛል? ሥራዬን ወይም ትምህርቴን ቸል ብያለሁ? በቤቴ ውስጥ ረድቻለሁ? አረጋውያንን እንቃለሁ? የሀገርን ሕግ ወይም እንደ ፖሊስ ያሉ ባለሥልጣናትን አልታዘዝም?

አምስተኛው ትእዛዝ፦ “አትግደል።”

ሰው ገድያለሁ? ፅንስ አስወርጃለሁ ወይም ሌላ ሰው ፅንስ እንዲያስወርድ ረድቻለሁ? የራሴን ወይም የሌላ ሰውን የአካል ክፍል ቆርጬ ወይም አጉድዬ አበላሽቻለሁ? ራሴን ለመግደል ሞክሬአለሁ ወይም ራሴን ስለመግደል በቁም ነገር አስቤአለሁ? በመጣላት ወይም ሌሎችን በመምታት ዓመፅ እፈጽማለሁ? የዘረኝነት ኃጢአት ፈጽሜአለሁ? በሌላ ሰው ላይ የጥላቻ ሐሳብ አሳድሬአለሁ? ሆን ብዬ በሌሎች ላይ ክፉና የበቀል ሐሳቦችን በውስጤ አቆያለሁ? ተበቅዬአለሁ? ሌላን ሰው በጭካኔ ወይም በስድብ ተናግሬአለሁ? ባለጌነት ወይም ነውር ያለበት ጠባይ አሳያለሁ፣ ወይም በሌሎች ላይ እሳለቃለሁ? ሕገወጥ አደንዛዥ ዕፆችን ተጠቅሜአለሁ ወይም በሐኪም ማዘዣ የሚሰጡ መድኃኒቶችን አላግባብ ወስጃለሁ? ሕገወጥ አደንዛዥ ዕፆችን ሸጫለሁ ወይም አሰራጭቻለሁ? ለሰውነቴ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ቸል እላለሁ? ከልክ በላይ እበላለሁ ወይም እተኛለሁ? የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ እጠጣለሁ? ራሴን ለመስከር ፈቅጃለሁ? ስለ ጤንነቴ ወይም ውጫዊ ገጽታዬ ከልክ በላይ እጨነቃለሁ? በእንስሳት ላይ እጨክናለሁ?

ስድስተኛው & ዘጠነኛው ትእዛዛት፦ “አታመንዝር። የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ።” 

ከትዳር ውጭ የፍቅር ግንኙነት አድርጌአለሁ? የትዳር ጓደኛዬን ከድቻለሁ ወይም ከሌላ ሰው የትዳር ጓደኛ ጋር አመንዝሬአለሁ? ከጋብቻ ውጭ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽሜአለሁ? ርኩስ ነገሮችን ተመኝቻለሁ ወይም ፈጽሜአለሁ? ርኩስ ሐሳቦችን ወይም ምኞቶችን በማሰላሰል ተደስቻለሁ? ርኩስ ጽሑፎችን አንብቤአለሁ፣ ርኩስ ግጥም ያላቸውን ዘፈኖች አዳምጫለሁ፣ ወይም በፎቶ፣ በቴሌቪዥን፣ በፊልም ወይም በኢንተርኔት ላይ ርኩስ ምስሎችን ተመልክቻለሁ? በርኩስ መሳሳም፣ መተቃቀፍ ወይም መዳሰስ በራሴ ወይም በሌላ ሰው ውስጥ የግብረ ሥጋ ፍላጎት አነሳስቻለሁ? ብቻዬን ርኩስ ድርጊት፣ ማለትም በእጅ የግብረ ሥጋ እርካታን መፈለግ፣ ፈጽሜአለሁ? ከተመሳሳይ ፆታ ጋር የግብረ ሥጋ ድርጊቶችን ወይም ሌሎች ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ ድርጊቶችን ፈጽሜአለሁ? በቀዶ ሕክምና፣ የዘር ፍሬ እንዳይገናኝ በሚከለክሉ መከላከያዎች ወይም በኬሚካል ዘዴዎች ሰው ሠራሽ የወሊድ መከላከያ እጠቀማለሁ? ልከኝነት የጎደለው ልብስ ለብሻለሁ ወይም ስለ ውጫዊ ገጽታዬ ከልክ በላይ ተጨንቄአለሁ? ብልግና ያለበት ንግግር እጠቀማለሁ፣ ወይም ርኩስ ቀልዶችንና ታሪኮችን እናገራለሁ ወይም አዳምጣለሁ?

ሰባተኛውና አሥረኛው ትእዛዛት፦ “አትስረቅ። የባልንጀራህን ንብረት አትመኝ።” 

የእኔ ያልሆነን ነገር ወስጃለሁ? የግል ወይም የሕዝብ ንብረት ጎድቻለሁ ወይም በእኩይ ድርጊት መልኩን አበላሽቻለሁ? ከሱቅ ዕቃ ሰርቄአለሁ? የተሰረቀ ንብረት ተቀብያለሁ ወይም ገዝቻለሁ፣ ወይም አንድን ሰው እንዲሰርቅ ረድቻለሁ? ለአንድ ሰው ጉቦ ሰጥቻለሁ? ያለባለቤቱ ፈቃድ የሆነ ነገር ተውሻለሁ? የተዋስሁትን ነገር ሳልመልስ ቀርቻለሁ? ገንዘብ አባክናለሁ ወይም ከልክ በላይ አወጣለሁ? ከልክ በላይ ቁማር እጫወታለሁ? ለገንዘብ ወይም ለዓለማዊ ንብረት ስግብግብነትን በውስጤ አሳድሬአለሁ? ገንዘብን ወይም ማንኛውንም ንብረት ሐሰተኛ አምላክ አድርጌአለሁ? ዕቃዎችን ወይም ምግብ አባክናለሁ? በፈተና ወይም በትምህርት ቤት ሥራ ላይ ኮርጄአለሁ? በጨዋታ ወይም በስፖርት ላይ አጭበርብሬአለሁ?

ስምንተኛው ትእዛዝ፦ “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።” 

ሆን ብዬ ዋሽቻለሁ? ሌሎችን በሐሰት ስም አጥፍቻለሁ? ስለ ሌሎች አማለሁ ወይም ሐሜት አዳምጣለሁ? እንድጠብቀው የተጠየቅሁትን ምሥጢር ተናግሬአለሁ? አንድ ሰው በእኔ ላይ ያደረገውን እምነት አፍርሻለሁ? ማንንም ሰው ፍቅር በጎደለው መንገድ ነቅፌአለሁ? በሌሎች ላይ በችኮላ እፈርዳለሁ፣ መሠረት የሌላቸውንም ጥርጣሬዎች በውስጤ አሳድራለሁ? ሆን ብዬ ማንንም ሰው አሳስቻለሁ ወይም አታልያለሁ? የእውነቱን ክፍል ብቻ ተናግሬ የቀረውን ደብቄአለሁ? ለአንድ ሰው ይቅርታ ለማድረግ እምቢ ብያለሁ ወይም ቂም ይዣለሁ? ያስቀየምሁትን ሰው ይቅርታ ሳልጠይቅ ወይም ጥፋቴን ሳላካክስ ቀርቻለሁ?

ሌሎች ልመረምራቸው የሚገቡ ነገሮች፦ ስግብግብ ወይም ራስ ወዳድ ነኝ? ወይስ ለራሴ በማዘን እጠመዳለሁ? ትዕቢተኛ ነኝ? በከንቱ እመካለሁ ወይስ ለታይታ እሠራለሁ? በውጫዊ ገጽታ ብቻ የምመራና በዓለማዊ ነገሮች የተጠመድሁ ነኝ? ስኬቴን አጋንኜ በመናገር ለመመስገን እፈልጋለሁ? ቶሎ እቀየማለሁ? ስሜቴስ ከልክ በላይ በቀላሉ ይነካል? ትንሽ መዘንጋትን ወይም ሳያስቡ ያደረጉትን ነገር አጋንኜ፣ እንደ ስድብ ወይም ሆን ብለው እንደናቁኝ እቆጥረዋለሁ? ጉራ ነዝቻለሁ? በሌሎች ላይ ትዕቢት አሳይቻለሁ? የራሴም ሆኑ የሌላ ሰው፣ ኃጢአት የሆኑ ድርጊቶችን በእልከኝነት ተከራክሬ ተሟግቻለሁ? ዓመፀኛ ነኝ? የበለጠ ጠቃሚ ነገር ማድረግ እየቻልሁ፣ ከቴሌቪዥን ፊት ተቀምጬ ጊዜዬን በከንቱ አሳልፌአለሁ? በሌላ ሰው ንብረት እቀናለሁ? የእኔ እንዲሆንስ ከልክ በላይ እመኛለሁ? በሌሎች ሰዎች መከራ ደስ ይለኛል?

የንስሐ ጸሎት

አምላኬ ሆይ፣ አንተን በመበደሌ ከልቤ አዝናለሁ። በፍትሐዊ ቅጣቶችህ ምክንያት ኃጢአቴን ሁሉ እጠላለሁ፤ ከሁሉ በላይ ግን፣ አምላኬ ሆይ፣ ፍጹም ቸር የሆንኸውንና ፍቅሬ ሁሉ የሚገባህን አንተን ስለሚበድሉ እጠላቸዋለሁ። በጸጋህ እርዳታ ከእንግዲህ ኃጢአት ላለመሥራትና ለኃጢአት የሚያቀርቡኝን አጋጣሚዎች ለመራቅ በጽኑ እወስናለሁ። አሜን።


የቅዱስ ሰዓት ጸሎት አደረጃጀት

ሕሊናን መመርመር፦ ሰባቱ ዋና ዋና ኃጢአቶች

ሕሊናን መመርመር፦ አሥርቱ ትእዛዛት

ለቅዱስ ሰዓት ጸሎት የሚሆን ሳምንታዊ የሕሊና ምርመራ

ሕሊናን መመርመር፦ እምነት፣ ተስፋ & ፍቅር

አጭር የሕሊና ምርመራ፦ እምነት፣ ተስፋ & ፍቅር

ዕለታዊ ጸሎቶች

የጠዋት ጸሎቶች

የከሰዓት በኋላ ጸሎት

በየምሽቱ የሚደረግ አጠቃላይ የሕሊና ምርመራ

ጥልቀቶችን መመርመር – ሙሉ የይዘት ማውጫ

ክፍል አንድ፦ የቅዱስ ኢግናጽዮስ የሕይወት ዳራ እና ከመንፈሳዊ ልምምዶች የሚገኙ ትምህርቶች

ክፍል ሁለት፦ በሥርዓተ አምልኮ ዓመት መሠረት የተደረደሩ የኢግናጽዮስ ማሰላሰያዎች

ክፍል ሦስት፦ ዓመቱን ሙሉ ለጸሎት የሚያገለግሉ ተጨማሪ ጽሑፎች