አማርኛ

መግቢያ

ለተጋቡ ጥንዶች በተዘጋጀ የሳምንት መጨረሻ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ላይ በመሳተፍና ትምህርት በማቅረብ ላይ ሳለሁ፣ ለባለቤቴ ደብዳቤ ለመጻፍ ጥቂት ጊዜ ወሰድሁ። ደብዳቤውን እየጻፍሁ ሳለ፣ በድንገት “ከፈቀድክልኝ ወደ ሕይወትህ መግባት እችላለሁ” የሚሉትን ቃላት እየተጠቀምሁበት በነበረው ማስታወሻ ደብተር ላይ ጻፍሁ። እንደጻፍኋቸውም ተደነቅሁ፣ በጥልቅም ተነካሁ፤ ምክንያቱም ለባለቤቴ እየጻፍሁት የነበረው ደብዳቤ ክፍል ሳይሆኑ፣ እግዚአብሔር በቀጥታ ለእኔ እየተናገረኝ ያለው ቃላት እንደሆኑ አወቅሁ። በዚያው ጊዜ፣ ከዚያ በፊት ፈጽሞ አጋጥሞኝ የማያውቅ እጅግ ጥልቅ የሆነ ሰላም ተሰማኝ።

ወደ ቤታችን ከተመለስን በኋላ፣ ራሴን አረጋግቼ፣ ጸልዬ፣ ማስታወሻ ደብተር አንሥቼ፣ ብዕር በእጄ ይዤ መጻፍ በጀመርሁ ቁጥር፣ መንፈሳዊ ሐሳቦችን መጻፍ መቀጠል ቻልሁ። በምጽፍበት ጊዜ፣ ቃላቱ በተለመደው ፍጥነቴ ከምጽፈው አምስት እጥፍ ያህል በሚፈጥን ፍጥነት የሚፈስሱ ይመስሉ ነበር። ከአእምሮዬ ስለሚወጣው ነገር ማሰብ እንኳ አላስፈለገኝም። ቃላቱ በራሳቸው ይፈስሱ ነበር። ከጊዜ በኋላ፣ እነዚህ ቃላት በግልጽ ሲነገሩኝ ሰማሁ፦ “መጽሐፍ ትጽፋለህ፣ ብዙዎችም ያነቡታል።”

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ጽሑፎች፣ ከዚያ ቀጥሎ ለብዙ ዓመታት ያደረግሁት ጥረት ውጤት ናቸው። ይህ ከእግዚአብሔር እንደሆነ አምናለሁ፤ ምክንያቱም ጥልቅ ሰላም ሲሰማህ፣ ይህ ከላይ የተሰጠ እንጂ ከዚህ ዓለም እንዳልሆነ በውስጥህ ታውቃለህ።  

ከዚህ ስጦታ ጋር ለብዙ ዓመታት ታግያለሁ፣ አሁንም እታገላለሁ። ይህ ስጦታ በውስጤ ታትሞ ነበር፣ እኔም ሁልጊዜ እንዳለ አውቅ ነበር። ፈጽሞ አልተለየኝም። ዘላቂ ነበር። በዚያ ጊዜ፣ በርካታ ጓደኞቼ እነዚህን መንፈሳዊ ሐሳቦች ከመጀመሪያው የማስታወሻ ደብተሬ በመውሰድ በማሽን ጻፉልኝ፤ ይዘቱን እንዴት ማሳተም እንደምንችል ግን መወሰን አልቻልንም። ተገቢው ጊዜ ሲደርስ እንዲረዳኝና መንገዱን እንዲያሳየኝ እግዚአብሔርን ለመንሁ። የማሳተሚያ መንገድ እስኪታይ ድረስ ሠላሳ ሰባት ዓመታት አለፉ። ይህ የተቀበልሁትን መመሪያ የሚያስፈጽም ስለሆነ፣ ለዚህ አመስጋኝ ነኝ።  

ይህ መጽሐፍ በብዙዎች ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት እንዲያገኝና የሚያነቃቃቸው ሐሳቦች ብዙ መልካም ጥቅሞችን እንዲያስገኙ ተስፋ አደርጋለሁ። በጊዜ ሂደት ከተቀበልኋቸው ምክሮች ሁሉ የሚበልጠው፣ በሚያፈራው ፍሬ እንድመዝነው የሚለው ነበር።

ይህ የመጻፍ ችሎታ በጥንቃቄና በአክብሮት መያዝ ያለበት፣ እውነተኛ የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ አውቃለሁ። ትዕቢት ሊገባ አይገባም፣ ትሕትናም ሊያሸንፍ ይገባል። ልንጠነቀቅበት የሚገባው ድክመት፣ የልብን ጥልቀት ከማዳመጥ ይልቅ የራስን ሐሳብ በውስጡ ማስገባት ነው። አንድ ቀን በመንፈስ ቅዱስ እየተመራሁ ይህን ጽሑፍ መቀጠል እንድችል እጸልያለሁ። ይህን ውሳኔ ለመንፈስ ቅዱስ አመራር እተዋለሁ።


መታሰቢያ

እነዚህን ጽሑፎች እንዳሳትም ላበረታታችኝ ባለቤቴ። ይህ መጽሐፍ የሚታተምበትን መንገድ ላመቻቸልኝ ልጄና ለቤተሰቤ አባላት ሁሉ። እኔን በማነቃቃት የራሷን ድርሻ ላበረከተችው፣ በሰማይ ላለችው ሴት ልጄ። እነዚህን ገጾች ላነበቡ፣ ላረሙና በእነዚህ ጽሑፎች ለተነቃቁ ጥቂት ወዳጆቼ።  

የመንፈስ ቅዱስን ቃላት የማዳመጥ ችሎታ ለሰጠኝ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ።

እነዚህ ጽሑፎች የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ያክብሩ።


በሮበርት ሬይመንድ

“ሮበርት ሬይመንድ” ይህ ደራሲ የመረጠው የብዕር ስም ነው፤ ሮበርት በምሥጢረ ሜሮን የተቀበለው ስም ሲሆን፣ ሬይመንድ ደግሞ የፔኛፎርቱን ቅዱስ ሬይመንድ በረከት በዚህ ሥራ ላይ ለመለመን የመረጠው ነው።

ቅዱስ ሬይመንድ ገና በሃያ ዓመቱ ፍልስፍና ያስተምር ነበር። በሠላሳዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ውስጥ በፍትሐ ብሔር ሕግና በቤተ ክርስቲያን ሕግ የትምህርት ዲግሪዎችን አግኝቶ ነበር። የቅዱስ ሬይመንድ ችሎታ እጅግ የላቀ ስለነበር፣ ነገሥታት፣ ጳጳሳተ ሮማና ጳጳሳት ሁሉ አገልግሎቱን ይጠይቁ ነበር። ጳጳስ ጎርጎርዮስ ዘጠነኛው የእርሱን ፈቃድ አገኙ፤ የፔኛፎርቱም ቅዱስ ሬይመንድ፣ እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ለቤተ ክርስቲያን ሕግ ባለሙያዎች መሠረታዊ ማጣቀሻ የሆነ እጅግ ሰፊ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ስብስብ በማዘጋጀት፣ ለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ አስተዋጽኦ አበረከተ።

ይህ ደራሲ በሕይወት ውስጥ በሚከሰቱ ነገሮች ላይ ልዩ ጥበቃ እየለመነ፣ ለብዙ ዓመታት በየቀኑ ወደ ቅዱስ ሬይመንድ የዘጠኝ ቀን ጸሎት ሲጸልይ ቆይቷል።

ቅዱስ ሬይመንድ ሆይ፣ በዚህ ሕይወት የሚገጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ ለመጋፈጥ በሚያስፈልገን ጥበብ ዛሬ አስተምረን፣ እርዳንም። በምልጃህ ደግፈን። ከዚህ ዓለም ወደሚጠብቀን ሰማያዊ መንግሥት በምንሸጋገርበት ጊዜ ከእኛ ጋር ሁን።

የቅጂ መብት © 2019 በሮበርት ሬይመንድ። መብቶች ሁሉ በሕግ የተጠበቁ ናቸው። ማንኛውም ቤተ ክርስቲያን ወይም ተቋም ለንግድ ላልሆነ ዓላማ እንደገና እንዲያትመው ፈቃድ ተሰጥቷል።


ማውጫ