አማርኛ

አሥራ አራተኛው ቀን – «የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ»


የቪዲዮ ቅጂ

የወይን ጠጁ ባለቀ ጊዜ፣ የኢየሱስ እናት፣ «የወይን ጠጅ የላቸውም» አለችው። [እናም] ኢየሱስ፣ «ሴት ሆይ፣ ያንቺ ጉዳይ እኔን እንዴት ይመለከተኛል? ሰዓቴ ገና አልደረሰም» አላት። እናቱም አገልጋዮቹን፣ «የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ» አለቻቸው። ዮሐንስ 2:3-5

ብፅዕት እናታችን፣ «የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ» የሚሉትን እነዚህን ቃላት የተናገረችው ኢየሱስ የመጀመሪያውን ተአምር ባደረገበት ጊዜ ነበር። እነዚህ ቃላት ጥልቅና ኃይለኛ ናቸው፤ በቀላሉም የመንፈሳዊ ሕይወታችን መሠረት ሊሆኑ ይችላሉ።

ብፅዕት እናታችን ከመስቀሉ ሥር ለልጇ አንድ ነገር ብትናገር ኖሮ፣ ምን ትል ነበር? የተስፋ መቁረጥ ወይም የግራ መጋባት፣ የሥቃይ ወይም የቁጣ ቃላትን ትናገር ነበርን? አይደለም፤ በቃና ሠርግ የተናገረቻቸውን ተመሳሳይ ቃላት ትናገር ነበር። በዚህ ጊዜ ግን እነዚህን ቃላት ለአገልጋዮቹ ሳይሆን ለልጇ ትናገራቸው ነበር። «በሙሉ ልቤ የምወድህ ውድ ልጄ ሆይ፣ የሰማዩ አባት የሚልህን ሁሉ አድርግ።»

በእርግጥ ኢየሱስ ይህን ምክር አላስፈለገውም፤ ሆኖም ከእናቱ ለመቀበል ፈለገ። እናቱ እነዚህን ፍጹም ፍቅር የተሞሉ ቃላት ስትናገረው ለመስማት ፈለገ። ብፅዕት እናታችንና መለኮታዊ ልጇ፣ እርሱ በመስቀል ላይ በሚሠቃይበት ጊዜ እርስ በርሳቸው እየተያዩ፣ በቃና አንድ ጊዜ የተነገሩትን እነዚህን ቃላት ሲያሰላስሉ ጥልቅ አንድነት ተካፍለው ይሆናል። እናትና ልጅ ሁለቱም የእርሱ ሞት ከቶ ታውቆ የማያውቀውን ከሁሉ የላቀ በጎ ነገር መፈጸም መሆኑን ያውቁ ነበር። የሰማዩ አባት ፈቃድ ፍጹም መሆኑን ሁለቱም አውቀው ይሆናል። ይህን ቅዱስ ፈቃድ ሁለቱም ናፍቀውትና ያለ ምንም ማመንታት ተቀብለውት ይሆናል። በዝምታ እርስ በርሳቸው ሲተያዩም እነዚህ ቃላት በሁለቱም ልብ ውስጥ ነበሩ ይሆናል፦

«ውድ እናቴ ሆይ፣ አባታችን የሚልሽን ሁሉ አድርጊ።»

«ውድ ልጄ ሆይ፣ የሰማዩ አባትህ እንድታደርገው የሚፈቅደውን ሁሉ አድርግ።»

ዛሬ እነዚህን ቃላት አሰላስል፤ እናትና ልጅም ለአንተ እንደሚናገሯቸው እወቅ። በሕይወትህ ምንም ነገር ቢገጥምህ፣ ብፅዕት እናታችንና መለኮታዊ ልጇ ይህን የከበረ የፍቅርና የታዛዥነት ትእዛዝ እንድትቀበል ይጋብዙሃል። በትግሎች ሁሉ ውስጥ፣ በመልካምም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ፣ በሥቃይም ሆነ በደስታ ውስጥ ታማኝ ሆነህ እንድትጸና ያበረታቱሃል። በሕይወትህ ምንም ነገር ቢያጋጥምህ፣ እነዚህ ቃላት ሁልጊዜ በአእምሮህና በልብህ ውስጥ ሊያስተጋቡ ይገባል። «የሚልህን ሁሉ አድርግ።» እነዚህን ቅዱስ ቃላት ለመስማትና ለመቀበል አታመንታ።

እጅግ ውድ እናት ሆይ፣ ፍጹም ጥበብ የተሞሉ ቃላትን ትሰጫለሽ። ውድ ልጆችሽ ሁሉ የሰማዩን አባት ፍጹም ፈቃድ እንዲቀበሉ ትጋብዣቸዋለሽ። እነዚህ ቃላት ለእኔ ብቻ የተነገሩ አይደሉም። በመጀመሪያ በልብሽ ጥልቅ ስፍራ ለአንቺ ተነግረዋል። አንቺም በተራሽ ይህን የፍቅር ትእዛዝ ለተገናኘሻቸው ሁሉ ገለጽሽ። በዝምታም ለገዛ መለኮታዊ ልጅሽ ተናገርሻቸው።

አፍቃሪ እናቴ ሆይ፣ እነዚህን ቃላት ስትነግሪኝ እንዳዳምጥሽ እርጂኝ። በጸሎትሽ ኃይል፣ በሕይወቴ የእግዚአብሔርን ፍጹም ፈቃድ እንድቀበል ለሚጠራኝ ለዚህ ጥሪ ምላሽ እንድሰጥ እርጂኝ።

ውድ ኢየሱሴ ሆይ፣ የምታዝዘኝን ሁሉ ለማድረግ እመርጣለሁ። ያለ ምንም ማመንታት ፈቃድህን እመርጣለሁ፤ ፈለግህን እንድከተልም እንደምትጋብዘኝ አውቃለሁ። በመስቀሉ መከራዎች ፈጽሞ ወደ ኋላ እንዳልል፣ ይልቁንም በፍጹም ፈቃድህ ኃይል እንድለወጥ አድርገኝ።

እናት ማርያም ሆይ፣ ጸልዪልኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

አሥራ አምስተኛ ቀን – የእግዚአብሔርን ቃል መስማትና መጠበቅ

ማውጫ

በኤሌክትሮኒክ መጽሐፍ & በለስላሳ ሽፋን በታተመ መጽሐፍ መልክ ይገኛል!