አማርኛ

የቅዱስ ፓትሪክ የደረት ጋሻ

ዛሬ ከራሴ ጋር አስተሳስራለሁ፣
የሥላሴን ኃያል ስም፣
ይህንኑ ስም በመጥራት፣
በአንድ ያሉትን ሦስቱን፣ በሦስትም ያለውን አንዱን።

ዛሬ ለዘላለም ከራሴ ጋር አስተሳስራለሁ፣
በእምነት ኃይል፣ የክርስቶስን ሰው መሆን፣
በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁን፣
ለድኅነቴ በመስቀል ላይ መሞቱን፣
ሽቱ ከተቀባው መቃብር በኃይል መነሣቱን፣
በሰማያዊው መንገድ ማረጉን፣
በፍርድ ቀን መምጣቱን፤*
ዛሬ ከራሴ ጋር አስተሳስራለሁ።

ከራሴ ጋር አስተሳስራለሁ፣
የኪሩቤልን ታላቅ ፍቅር ኃይል፣
በፍርድ ሰዓት የሚሰማውን ጣፋጭ «መልካም አደረግህ»፣
የሱራፌልን አገልግሎት፣
የእምነት መስካሪዎችን እምነት፣ የሐዋርያትን ቃል፣
የአበውን ጸሎቶች፣ የነቢያትን ጥቅልሎች፣
ለጌታ የተደረጉትን መልካም ሥራዎች ሁሉ፣
የደናግል ነፍሳትንም ንጽሕና።

ዛሬ ከራሴ ጋር አስተሳስራለሁ፣
በከዋክብት ያጌጠውን ሰማይ ኃይሎች፣
የክብር ፀሐይን ሕይወት ሰጪ ጨረር፣
በምሽት የሚታየውን የጨረቃ ንጣት፣
በነፃነት የሚብለጨለጨውን መብረቅ፣
የሚሽከረከረውን ነፋስ ኃይለኛ ምቶች፣
ጽኑዋን ምድር፣ ጥልቁን ጨዋማ ባሕር፣
ጥንታዊና ዘላለማዊ አለቶችን የከበበውን።

ዛሬ ከራሴ ጋር አስተሳስራለሁ፣
የእግዚአብሔርን ኃይል፣ እንዲደግፈኝና እንዲመራኝ፣
ዓይኑን፣ እንዲከታተለኝ፤ ብርታቱን፣ እንዲያጸናኝ፣
ጆሮውን፣ የሚያስፈልገኝን እንዲሰማ።
የአምላኬን ጥበብ፣ እንዲያስተምረኝ፣
እጁን፣ እንዲመራኝ፤ ጋሻውን፣ እንዲከላከልልኝ፣
የእግዚአብሔርን ቃል፣ የምናገረውን እንዲሰጠኝ፣
ሰማያዊ ሠራዊቱን፣ ጠባቂዬ እንዲሆን።

የአጋንንት ወጥመዶች ከሆኑት ኃጢአቶች፣
ለፈተና ኃይል ከሚሰጠው መጥፎ ልማድ፣
በውስጤ ከሚዋጉት ተፈጥሯዊ ምኞቶች፣
መንገዴን ከሚያሰናክሉ ጠላቶች፤
ጥቂቶችም ይሁኑ ብዙዎች፣ ሩቅም ይሁኑ ቅርብ፣
በሁሉም ስፍራና በሁሉም ሰዓት፣
ከኃይለኛ ጥላቻቸው እንዲከላከሉልኝ፣
እነዚህን ቅዱሳን ኃይሎች ከራሴ ጋር አስተሳስራለሁ።

ከሰይጣን ድግምቶችና ተንኮሎች ሁሉ፣
ከመናፍቅነት ሐሰተኛ ቃላት፣
ከሚያረክስ እውቀት፣
ከልብ ጣዖት አምልኮ፣
ከጠንቋይ ክፉ ጥበብ፣
ከገዳይ ቁስልና ከእሳት ቃጠሎ፣
ከሚያሰጥም ማዕበልና መርዝ ከተቀባ ፍላጻ፣
ክርስቶስ ሆይ፣ እስክትመለስ ድረስ ጠብቀኝ።

ክርስቶስ ከእኔ ጋር ይሁን፣ ክርስቶስ በውስጤ፣
ክርስቶስ ከኋላዬ፣ ክርስቶስ ከፊቴ፣
ክርስቶስ ከጎኔ፣ ክርስቶስ ለራሱ እንዲያደርገኝ፣
ክርስቶስ እንዲያጽናናኝና እንዲያድሰኝ።
ክርስቶስ ከበታቼ፣ ክርስቶስ ከበላዬ፣
ክርስቶስ በሰላም ጊዜ፣ ክርስቶስ በአደጋ ጊዜ፣
ክርስቶስ በሚወዱኝ ሁሉ ልብ፣
ክርስቶስ በወዳጅና በእንግዳ አፍ ይሁን።

ስሙን ከራሴ ጋር አስተሳስራለሁ፣
የሥላሴን ኃያል ስም፣
ይህንኑ ስም በመጥራት።
በአንድ ያሉትን ሦስቱን፣ በሦስትም ያለውን አንዱን፣
ተፈጥሮ ሁሉ ፍጥረቱን ከእርሱ ያገኘውን፣
ዘላለማዊውን አብ፣ መንፈስን፣ ቃልን፤
ለድኅነቴ ጌታ ምስጋና ይሁን፣
ድኅነት ከጌታ ክርስቶስ ነው።

አሜን።

ተለይቶ የቀረበው ምስል በሎረንስ ኦፒ፣ ፍሊከር


ተጨማሪ ጸሎቶች>>>

ስለ ቅዱስ ፓትሪክ ተጨማሪ መረጃ>>>