ጥያቄ፦ እኔ ሰዎች በመኪኖቻቸው የኋላ እይታ መስታወት ላይ መቁጠሪያ ሲያንጠለጥሉ አይቻለሁ፤ አንዳንድ ሰዎችም መቁጠሪያ በአንገታቸው ያደርጋሉ። እንዲህ ማድረግ ተገቢ ነውን?
መልስ፦ በመጀመሪያ፣ ቀላል መልስ ልስጥና እነዚህን ድርጊቶች ተገቢ ናቸው ብዬ እንደማስብ ልናገር። አምላክን የሚያመልኩ፣ ጌታችንን እና ብፅዕት እናቱን የሚወዱ፣ በመኪኖቻቸውም የኋላ እይታ መስታወት ላይ መቁጠሪያ የሚያንጠለጥሉ ብዙ ሰዎችን አውቃለሁ። ለእነርሱ ይህ፣ ለማርያም ያላቸውን ፍቅር ሁሉም እንዲያይ የሚገልጡበት መንገድ ነው። በአንገታቸው ስለሚያደርጉትም ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል። አንድ ሰው ከእነዚህ ሁለቱ ድርጊቶች አንዱን ለማድረግ ቢመርጥ፣ ምናልባት ይህን የሚያደርገው ለብፅዕት እናታችን ካለው አምልኮና ፍቅር የተነሣ ነው። እኔ መቁጠሪያዬን በመስታወቴ ላይ ባላንጠለጥለውም፣ በአንገቴም ባላደርገውም፣ ሁልጊዜ በኪሴ እይዘዋለሁ። ማታ በእጄ አንጓ ላይ ጠምጥሜው እተኛለሁ። መቁጠሪያን በአቅራቢያችን ማኖር፣ መስቀል ወይም ስካፑላር እንደመልበስ፣ ወይም በክፍላችን ውስጥ ቅዱስ ሥዕል እንደማንጠልጠል ያለ ይመስለኛል። መቁጠሪያዎች የተባረኩ ዕቃዎች ናቸው፤ በዚህም ምክንያት በአቅራቢያችን ቢኖሩ መልካም ነው።
ጸሎተ መቁጠሪያ ከሁሉ በፊትና በዋነኝነት የጸሎት መሣሪያ፣ እንዲሁም ልንጸልያቸው ከምንችላቸው እጅግ መልካም ጸሎቶች አንዱ መሆኑም ሊነገር ይገባል። ስለ ጸሎተ መቁጠሪያ በራሴ ቃላት ከማብራራ ይልቅ፣ ታላላቅ ቅዱሳን ስለ እርሱ ከተናገሯቸው እኔ በጣም ከምወዳቸው አባባሎች ጥቂቶቹን ላቅርብላችሁ።
“ጸሎተ መቁጠሪያውን በየቀኑ የሚጸልይ ሰው ፈጽሞ አይሳሳትም። ይህ በደሜ በደስታ የምፈርምበት መግለጫ ነው።” ቅዱስ ሉዊስ ደ ሞንፎር
“ከጸሎቶች ሁሉ የመቁጠሪያ ጸሎት እጅግ ውብና በጸጋ እጅግ የበለጸገ ነው…የመቁጠሪያ ጸሎትን ውደዱ፤ በየቀኑም በትጋት ጸልዩት።” ቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 10ኛ
“በየምሽቱ የመቁጠሪያ ጸሎትን የሚጸልይ ቤተሰብ እንዴት ያማረ ነው!” ቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ
“የመቁጠሪያ ጸሎት ከሁሉ የምወደው ጸሎት ነው። ድንቅ ጸሎት ነው! በቀላልነቱም ሆነ በጥልቀቱ ድንቅ ነው።” ቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ
“የመቁጠሪያ ጸሎት በእግዚአብሔር መንፈሳዊ ምሪት የተሰጠ ዋጋው የማይተመን ሀብት ነው።” ቅዱስ ሉዊ ደ ሞንፎር
“በቤተሰብ ላይ የእግዚአብሔርን በረከት ለማሰፈን… በየቀኑ የመቁጠሪያ ጸሎትን ከመጸለይ ይልቅ የተረጋገጠ መንገድ የለም።” ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ
“የመቁጠሪያ ጸሎት ከሁሉ የላቀ የጸሎት ዓይነትና የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት እጅግ ውጤታማ መንገድ ነው። ለክፉ ነገሮቻችን ሁሉ መድኃኒት፣ ለበረከቶቻችንም ሁሉ ሥር ነው። ከእርሱ የሚልቅ የጸሎት መንገድ የለም።” ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ
“የመቁጠሪያ ጸሎትን የሚጸልይ ሠራዊት ስጡኝ፤ ዓለምንም ድል አደርጋለሁ።” ብፁዕ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 9ኛ
በልባችሁ፣ በቤታችሁና በአገራችሁ ሰላም ከፈለጋችሁ፣ የመቁጠሪያ ጸሎትን ለመጸለይ በየምሽቱ ተሰብሰቡ። በብዙ ጭንቀቶችና ሥራዎች ምንም ያህል ብትከበዱ፣ ሳትጸልዩት አንዲት ቀን እንኳ እንድታልፍ አትፍቀዱ።” ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ
“በመቁጠሪያ ጸሎት አማካይነት የለመንኳትን ጸጋ እመቤታችን ፈጽሞ ነፍጋኝ አታውቅም።” የፒየትሬልቺናው ቅዱስ (አባ) ፒዮ
“ከሁሉ የላቀው የጸሎት መንገድ የመቁጠሪያ ጸሎትን መጸለይ ነው።” ቅዱስ ፍራንስዋ ደ ሳል
“አንድ ቀን፣ በመቁጠሪያ ጸሎትና በስካፑላር አማካይነት፣ እመቤታችን ዓለምን ታድናለች።” ቅዱስ ዶሚኒክ
