
እጅግ ኃያል ድንግልና የምሕረት እናት፣ የሰማይ ንግሥትና የኃጢአተኞች መጠጊያ የሆንሽ ማርያም ሆይ፣ ራሳችንን እንከን ለሌለበት ልብሽ እንወስናለን።
ማንነታችንንና መላ ሕይወታችንን፣ ያለንን ሁሉ፣ የምንወደውን ሁሉና ሁለንተናችንን ለአንቺ እንወስናለን። ሥጋችንን፣ ልባችንንና ነፍሳችንን ለአንቺ እንሰጣለን፤ ቤቶቻችንን፣ ቤተሰቦቻችንንና አገራችንን ለአንቺ እንሰጣለን።
በውስጣችንና በዙሪያችን ያለው ሁሉ የአንቺ እንዲሆንና ከእናታዊ በረከትሽ ጥቅሞች እንዲካፈል እንመኛለን። ይህ ራሳችንን የመወሰን ተግባር በእውነት ፍሬያማና ዘላቂ እንዲሆንም፣ በጥምቀታችንና ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዱስ ቁርባንን በተቀበልንበት ጊዜ የገባናቸውን ቃሎች ዛሬ በእግርሽ ሥር እናድሳለን።
የቅዱስ እምነታችንን እውነቶች በድፍረትና በሁሉም ጊዜ ለመመስከር፣ እንዲሁም ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱና ከእሳቸው ጋር በኅብረት ላሉት ጳጳሳት መመሪያዎች ሁሉ በሚገባ የሚታዘዙ ካቶሊካውያንን በሚመጥን መንገድ ለመኖር ቃል እንገባለን።
የእግዚአብሔርንና የቤተ ክርስቲያኑን ትእዛዛት ለመጠበቅ፣ በተለይም የጌታን ቀን በቅድስና ለማክበር ቃል እንገባለን።
እንዲሁም በቻልነው መጠን የክርስትና ሃይማኖትን አጽናኝ ልምምዶች፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቅዱስ ቁርባንን መቀበል፣ የሕይወታችን የማይነጠል ክፍል ለማድረግ ቃል እንገባለን።
በመጨረሻም፣ ክብርት የእግዚአብሔር እናትና አፍቃሪ የሰው ልጆች እናት ሆይ፣ እንከን በሌለበት ልብሽ ንግሥና አማካይነት፣ ስግደት የሚገባው ልጅሽ የቅዱስ ልቡ መንግሥት በራሳችን ልብና በሰዎች ሁሉ ልብ፣ በአገራችንና በዓለም ሁሉ፣ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድር እንዲመጣ ለማፋጠንና ለማረጋገጥ፣ ለአንቺ የሚቀርበውን የተባረከ አክብሮት ለማገልገል ራሳችንን በሙሉ ልባችን እንደምንሰጥ ቃል እንገባልሻለን።
አሜን።