ጥ. በየቀኑ መጸለይ አለብኝ?
መ. እነዚህንም ጥቂት ተጨማሪ ጥያቄዎች መጠየቅ ይቻላል፦ «በየቀኑ መብላት አለብኝ?» «በየቀኑ መተኛት አለብኝ?» «በየቀኑ ጥርሴን መቦረሽ አለብኝ?» አንድ ሰው ለአንድ ቀን፣ ምናልባትም ከዚያ በላይ፣ እነዚህን ሳያደርግ ሊቆይ ይችላል፤ ነገር ግን ውጤቱን አይወደውም፣ ጉዳትም ሊያደርስበት ይችላል። ሰው ካልጸለየ፣ በራሱ ላይ ብቻ የሚያተኩር፣ ራስ ወዳድና በድብርት የተያዘ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ከሚያስከትላቸው ውጤቶች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ምናልባትም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ዘወትር እንዲጸልዩ የሚያዝዘው ለዚህ ይሆናል።
ክርስቶስ ደግሞ አንድ ሰው ሲጸልይ ወደ ውስጠኛው ክፍሉ ገብቶ ብቻውን መጸለይ እንዳለበት ለደቀ መዛሙርቱ ይነግራቸዋል። ሆኖም ክርስቶስ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በስሙ ሲሰበሰቡ በዚያ እንደሚገኝም ይናገራል። ክርስቶስ የሚፈልገው የግል ጸሎትንም የጋራ ጸሎትንም ነው። ጸሎት፣ የግልም ሆነ የጋራ፣ በብዙ መልኮች ሊቀርብ ይችላል፦ ቡራኬና ስግደት፣ ልመና፣ ምልጃ፣ ውዳሴና ምስጋና። በእነዚህ ሁሉ መልኮች ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ውይይት ነው። አንዳንድ ጊዜ መነጋገር ነው፤ ብዙ ጊዜ ግን ማዳመጥ ነው። የሚያሳዝነው፣ ብዙ ሰዎች ጸሎት ማለት የሚፈልጉትን ወይም የሚያስፈልጋቸውን ለእግዚአብሔር መንገር እንደሆነ ያስባሉ። እነዚህ ሰዎች የሚፈልጉትን ሳያገኙ ሲቀሩ ቅር ይላቸዋል። ስለዚህ ጸሎትን፣ እግዚአብሔር ለእርስዎ የሚፈልገውን እንዲገልጽልዎ እድል የሚሰጡበት ውይይት አድርጎ ማየት አስፈላጊ ነው።
አንድ ሰው «ከቅርብ ወዳጄ ጋር በየቀኑ መነጋገር አለብኝ?» ብሎ ይጠይቃልን? በፍጹም አይጠይቅም! ምክንያቱም ሰው ብዙውን ጊዜ ወዳጅነቱን ለማጠናከር ከወዳጁ ጋር ለመነጋገር ይናፍቃል። እንዲሁም እግዚአብሔር ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ይበልጥ እንዲቀርቡ ይፈልጋል። ይህም በጸሎት ይሆናል። አንድ ሰው በየቀኑ መጸለይን ከተለማመደ፣ ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ ይቀርባል፣ በሰማይ ወዳሉት ቅዱሳንም ይበልጥ ይቀርባል። በራሱ ላይ ያለው ትኩረትም እየቀነሰ፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለው ትኩረት ይበልጥ ይጨምራል።
ስለዚህ፣ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይጀምሩ! በአንድ ቀን ብዙ ለማድረግ አይሞክሩ። ጸሎትም እንደ አካል እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ ማደግ ያስፈልገዋል። ሰውነቱ ያልተለማመደ ሰው የአካል እንቅስቃሴ በሚጀምርበት የመጀመሪያ ቀን ማራቶን መሮጥ አይችልም። አንዳንድ ሰዎች በቅዱስ ቁርባን ፊት ሌሊቱን ሙሉ በጸሎት መትጋት ሳይችሉ ሲቀሩ ተስፋ ይቆርጣሉ። ከካህን ጋር ተነጋግረው ዕቅድ ያውጡ። ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ከቻሉ፣ ገብተው ለአምስት ደቂቃ ያህል ለስግደት ለመቆየት ይሞክሩ። በየቀኑ የሚደግሙትን የጠዋት ጸሎት ያግኙና ይጸልዩ፤ ቀንዎንም ገና ሲጀምሩ ለክርስቶስ ይስጡት። ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ በተለይም ከወንጌላትና ከመዝሙረ ዳዊት፣ አንድ ክፍል ያንብቡ። ክፍሉን ሲያነቡ፣ እግዚአብሔር ለሚነግርዎ ቃል ልብዎን እንዲከፍትልዎ በቀላሉ ይለምኑት። የመቁጠሪያ ጸሎትን ለመጸለይ ይሞክሩ። መጀመሪያ ላይ ይህ ትንሽ ከብዶ ከታየዎት፣ አንድ አሥርት ብቻ ለመጸለይ ይሞክሩ። ማስታወስ ያለብዎት አስፈላጊው ነገር፣ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ጌታ ሲናገር ለመስማት ማዳመጥ ነው። እርስዎ ሲናገሩም፣ እግዚአብሔር ሌሎችን፣ በተለይም የታመሙትንና የሚሠቃዩትን፣ በመንጽሔ ያሉትን ነፍሳትም ጨምሮ፣ እንዲረዳ በመለመን ላይ ያተኩሩ።
ጄ ኤል
