አማርኛ

ጥ. ለልጆችና ለታዳጊዎች የሚቀርቡ የመገናኛ ብዙኃን ይዘቶች

ጥያቄ፦ ዛሬ ልጆቻችንና ታዳጊዎቻችን ስለሚጠቀሙባቸው የመገናኛ ብዙኃን ምን ያስባሉ? ስለ መጻሕፍትስ? ስለ ፊልሞችስ? እውነተኛውን ሕይወት የሚያሳዩ ከሆነ፣ ስለዚያ ምን ይላሉ?

መልስ፦ መጻሕፍት፣ ፊልሞች፣ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ኢንተርኔት… ዛሬ በየቀኑ የምንዝናናባቸው፣ መረጃ የምናገኝባቸው፣ አንዳንዶች እንደሚሉትም በመልእክቶች «የምንደበደብባቸው» ብዙ መንገዶች አሉ። ከእነዚህ ሁሉ የመገናኛ ዓይነቶች ከአንድ መቶ ዓመት እጅግ በላይ የቆዩት መጻሕፍት ብቻ መሆናቸውን ማሰብ አስገራሚ ነው! ሌሎቹ ሁሉም የዘመናዊ መገናኛ ዓይነቶች ለሰው ኅብረተሰብ በቅርቡ የመጡ አዳዲስ ነገሮች ናቸው። እነዚህ አዳዲስ የመገናኛ ብዙኃን ዛሬ በእኛ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ እያሳደሩ እንደሆነ ብዙ ጊዜ አስባለሁ።

ስለ እነዚህ የአሁኑ ዘመን የመገናኛ ብዙኃን አስተያየቴን ጠይቀዋል። በተለይም መጻሕፍትና ፊልሞች «እውነተኛውን ሕይወት ሲያሳዩ» ምን እንደማስብ ጠይቀዋል። ጥቂት ሐሳቦችን ላቅርብ።

በመጀመሪያ የማቀርበው ሐሳብ፣ መጻሕፍትና ፊልሞች ምናብን ለማነቃቃትና ስሜቶችን ለመቀስቀስ ከፍተኛ አቅም አላቸው የሚል ነው። የሚያዝናኑትም ለዚህ ነው! ምናብና ስሜቶች ከእውነት ጋር ተስማምተው ወደ በጎነት ሲነቃቁ፣ ይህ መልካም ሊሆን ይችላል። ሆኖም መጻሕፍትና ፊልሞች ምናባችንንና ስሜቶቻችንን በማይጠቅም መንገድም ሊቀሰቅሱ ይችላሉ።

መጽሐፉ ወይም ፊልሙ በእውነተኛ ሕይወት ላይ የተመሠረተ ቢሆንስ? «በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ» መሆኑ ብቻ ተቀባይነት ያለውና የሚጠቅም ያደርገዋልን? በእኔ አስተያየት፣ አያደርገውም። አንድ ነገር በዓለማችን እውነታ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ብቻ የግድ ለእኛ የሚጠቅም ነው ማለት አይደለም። በዓለማችን ውስጥ «እውነተኛ» የሆኑ፣ ነገር ግን በእነሱ መዝናናት ይቅርና እነሱን በማሰብ ጊዜ ማሳለፍ እንኳ የማይገባባቸው ብዙ ነገሮች አሉ።

ከሎዮላው ቅዱስ ኢኛስዮስ ሕይወት አንድ ምሳሌ ላቅርብ። ቅዱስ ኢኛስዮስ ወደ እግዚአብሔር ከመመለሱ በፊት፣ ዝናና ክብር ስላተረፉ ታላላቅ ፈረሰኞች ታሪኮችን ማንበብ ይወድ ነበር። እንዲሁም ስለ ፈረሰኞች ጀግንነትና ጨዋነት እንዲሁም ስለ ፍቅር የሚተርኩ ታሪኮችን ይወድ ነበር። እነዚህን ሲያነብ ይነሳሳ ነበር፤ እንደ እነርሱ ዝናና ክብር ማግኘት፣ በሌሎች ዘንድ መከበርና የንጉሡ ቤተ መንግሥት ክበብ አባል የሆነች አንዲት ባላባት ሴት ልብን በፍቅር መማረክ ምን እንደሚመስልም ያስብ ነበር። አንድ ቀን ኢኛስዮስ በጦርነት ቆሰለ፤ ለማገገምም ለወራት በአልጋ ላይ ቆየ። የሚወዳቸውን መጻሕፍት እንዲያመጡለት ጠየቀ፤ ሆኖም የተገኘው «የክርስቶስ ሕይወት» የሚል መጽሐፍና ስለ ቅዱሳን የሚተርክ መጽሐፍ ብቻ ነበር። እነዚህን መጻሕፍት ሲያነብ በጥልቅ ተነሳሳ፤ ቅዱስ መሆን ምን እንደሚመስልም ማሰብ ጀመረ። ከዚያም በሁለቱ የመጻሕፍት ዓይነቶችና በእርሱ ላይ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ መካከል ያለውን ልዩነት አስተዋለ። ስለ ፈረሰኞችና ፍቅር የሚተርኩትን ታሪኮች ሲያነብ፣ ወዲያውኑ ስሜቱ ይነቃቃና ይነሳሳ ነበር፤ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ውስጡ ባዶነትና እረፍት ማጣት ይሰማው ነበር። የቅዱሳንን ታሪኮች ሲያነብም እንዲሁ እጅግ ይነሳሳ ነበር። ልዩነቱ ግን እነዚህን መጻሕፍት ሲያነብ፣ ያገኘው መነሳሳትና እንደ ቅዱሳኑ ለመኖር የነበረው ጉጉት ባዶነትና እረፍት ማጣት ሳይሆን፣ ሰላምና እርካታ ይተውለት ነበር።

ለእናንተ የምሰጠው ምክር ይህ ነው። ወደ አእምሯችን የምናስገባው ነገር ተጽዕኖ ያሳድርብናል። በሐዘን የተሞላውንና በኃጢአት የወደቀውን ዓለማችንን እውነታ ብቻ ከሚያሳዩ ይልቅ፣ እንደ ክርስቲያኖች እንድንኖርባቸው የተጠራንባቸውን በጎ ምግባሮች የሚያሳዩ መጻሕፍትንና ፊልሞችን ፈልጉ። አንድ ዓይነት ፊልም ወይም መጽሐፍ ጠቃሚ መሆኑን እርግጠኞች ካልሆናችሁ፣ በእናንተ ወይም በልጆቻችሁ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ተመልከቱ። ኢኛስዮስ እንደተገነዘበው፣ ለማንበብ ወይም ለመመልከት የሚገባ ማንኛውም ነገር ዘላቂ ሰላምና እርካታ ሊተውልን ይገባል።


ተጨማሪ ካቶሊካዊ ጥያቄዎችና መልሶች