አማርኛ

ጥያቄ፦ እንስሳት ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

ጥያቄ፦ እንስሳት ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

መልስ፦ እያንዳንዱ ካህን ይህን ጥያቄ ከልጆች ይሰማል! ልጆች፣ እንዲሁም ሰዎች ሁሉ፣ ለቤት እንስሳቶቻቸው ያላቸው ጥልቅ ፍቅር፣ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ «አዎን» እንዲሆን አጥብቀው እንዲመኙ የሚያደርጋቸው ይመስላል። ስለዚህ መልሱ… «አዎን»፣ «ምናልባት»፣ «በትክክል እንዲህ ማለት አይቻልም» እና «ተስፋ ማድረግ ትችላለህ!» የሚል ነው።

ይህ አስቸጋሪ ጥያቄ ግልጽና ቁርጥ ያለ መልስ የለውም። ስለዚህ ከላይ ከተሰጡት መልሶች ማንኛውም ትክክል ሊሆን ይችላል። ሆኖም፣ ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወትና ስለ እንስሳት ጥቂት ማብራሪያዎችንና ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን እናቅርብ።

በመጀመሪያ፣ እኛ ሰዎች ስንሞት፣ ማለትም ኢየሱስ «አዲሱን ሰማይና አዲሲቱን ምድር» ለማቋቋም ከመመለሱ በፊት ባለው በዚህ የታሪክ ዘመን ስንሞት፣ ሥጋችንና ነፍሳችን እንደሚለያዩ እናምናለን። ኢየሱስ በክብሩ ሁሉ ተመልሶ የሥጋን ትንሣኤ እስኪያመጣ ድረስ፣ ሥጋ ይሞታል፣ «በዕረፍትም ይቀመጣል»። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሥጋ ሙት ነው። የሰዎች መንፈሶች ግን በሕይወት ይቀጥላሉ። መንፈሳችን ሊሞት አይችልም፤ ስለዚህም ከምድራዊ ሞት በኋላ ሰማይ፣ ወይም መንጽሔ እሳት፣ ወይም ገሃነም መንፈሳችንን ይጠብቃል። ዘላለማዊ መንፈስ ያላቸው ሰዎች፣ መላእክትና እግዚአብሔር ብቻ ናቸው። እንስሳት ግን የላቸውም። ስለዚህ፣ በአሁኑ ጊዜ አንድ እንስሳ ሲሞት፣ ሙት ነው፤ በሰማይ በሕይወት የሚቀጥል መንፈስም የለውም።

ግን አንድ አፍታ ጠብቅ! የቤት እንስሳህና ፍጥረታት ሁሉ እንደገና እንዲነሡ ተስፋ አለ። እንዴትና ለምን? ይህን ተስፋ ማድረግ የምትችልበት ምክንያት፣ ከዘመን መጀመሪያ አንሥቶ፣ በመጀመሪያው የቅድስና ሁኔታ ውስጥ፣ ማለትም በኤደን ገነት፣ እንስሳት ስለነበሩ ነው። ስለዚህ፣ እንስሳት ዘላለማዊ መንፈስ ባይኖራቸውም፣ አካላዊ ፍጥረታት ናቸው፤ የእንስሳ ነፍስ ልንለው የምንችለውም አላቸው። እንስሳው ሲሞት የእንስሳው ነፍስም በእርግጥ ትሞታለች፤ በሙታን ትንሣኤ ግን ምን ሊሆን እንደሚችል መናገር አይቻልም! ኢየሱስ በክብሩ ሁሉ ሲመለስና ሰዎች ሁሉ ከሙታን ሲነሡ፣ እንስሳትና ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ሁሉም ይነሡ ይሆን? ይህ ተስፋ ልታደርግበት የምትችለው ነገር ነው።

በተጨማሪም፣ ኢሳይያስ 11:6 ስለዚህ ስለሚመጣው አዲስ ዘመን በትንቢት ይናገራል። ያ ክፍል እንዲህ ይላል፦ «በዚያን ጊዜ ተኩላው የበጉ እንግዳ ይሆናል፣ ነብሩም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤ ጥጃውና ወጣቱ አንበሳ አንድ ላይ ይሰማራሉ፣ ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል።» ታዲያ ይህ በቀጥተኛ ትርጉሙ የሚወሰድ ንግግር ነው? እንስሳት እንደሚነሡ ማረጋገጫ ነው? ወይስ ተምሳሌታዊና ምሳሌያዊ አነጋገር ብቻ ነው? ለመናገር ያስቸግራል። ሆኖም፣ በዚህ ምክንያት እንስሳት በሚመጣው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የሆነ ድርሻ ይኖራቸዋል ብሎ ተስፋ ማድረግ ተገቢ ነው!


ተጨማሪ ካቶሊካዊ ጥያቄዎችና መልሶች